“ምን ለብሳ ነበር?”

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
09:09 ደቂቃ
07.12.2018

የሴቶች አለባበስና እና አስገድዶ መድፈር

ስትደፈር ምን ለብሳ ነበር በሚል በትዕይንቱ ላይ ዕድሜያቸው ከሰባት እስከ 20 ዓመት ያሉ የ15 ሴቶች ልብስ እና ታሪካቸው ለተመልካች ቀርቧል።

“ከክፍለ ሀገር ሥራ ለመሥራት ብዬ ነው ከቤት ጠፍቼ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት። መንገድ ላይ ፖሊሶች አገኙኝና ወደ ጣቢያ ወስደው ተረኛ የነበረውን ፖሊስ የሴቶች እስር ቤት ውስጥ አሳድራትና ሰኞ ጉዳዮን እናያለን ብለውት ሄዱ..... ከዛ ግን ፖሊሱ ቢሮው ውስጥ አስገብቶ ደፈረኝ። ሲነጋ እስረኞች ጋር ወስዶ አስገባኝ። ለማንም አልናገርም ብዬ ነበር ግን እዛ ውስጥ የነበሩት እስረኞች ፖሊሶቹ ሲመጡ ይቺ ልጅ ሲነጋ ነው የመጣችው የት እንዳደረች ጠይቋት ብለዋቸው ሲጠይቁኝ ነገርኳቸው። ጥቃቱን ያደረሰብኝ ፖሊስ መጀመሪያ ታስሮ ነበር ግን በዋስ ተለቀቀና ጠፋ..... እስካሁን አልተያዘም። ፖሊስ ጣቢያ ባልሄድ ኖሮ ይህ አይፈጠርም ነበር እያልኩ አንዳንዴ አስባለሁ።” 
«ምን ለብሳ ነበር« በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ቤተ መዘክር በመታየት ላይ በሚገኘው አውደ ርዕይ ላይ የቀረበ የአንድ የ16 ዓመት አዳጊ ወጣት ታሪክን ነው። 
አንዲት ሴት ተደፍራ ሳለ፤ «የት ነበርሽ?» «ምን ለብሰሽ ነበር?» የሚሉ ጥያቄዎችን ማቅረብ ለወንጀሉ መፈፀም ትልቁን ሚና እሷ እንደተጫወተች ያህል የሚያቀርቡ ወገኖች ፤ የወንጀል ፈጻሚውን ጥፋት ለመከላከል ይመስላል የሚሉ ጥቂት አይደሉም። «ምን ለብሳ ነበር» በሚል ርዕስ የቀረበው እጅጉን የሚያሳዝን እና ልብ የሚነካ ትዕይንት ነው ይላሉ የአውደ ርዕዩ ተመልካቾች። ዶ/ር ፌቨን ጌታቸው ከተመለከቱት አንዷ ናት።
«ልብሳቸው ተቀምጦ ታሪካቸውን ስታነቢ ከታሪክበት ያልፋል እውነታውን ትረጅዋለሽ።»
«ኤግዚቢሽኑ የሚያሳዝንና የሚያስፈራ ነበር። የነበሩት ነገሮች ሴቷ ለብሳ የነበረው ለዛ የሚጋብዝ እንዳልሆነ በደንብ ያሳያል።»
«ምን ለብሳ ነበር» ሴታዊት የሴቶች ንቅናቄ ማሕበር በኢትዮጵያ ከሲዊድን ኤምባሲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው አውደ ርዕይ ነው። ከኅዳር 17 እስከ ታህሳስ 1 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ

ሙዚየም ለተመልካች ቀርቦ እየታየ ይገኛል። ስትደፈር ምን ለብሳ ነበር በሚል በትዕይንቱ ላይ ዕድሜያቸው ከሰባት እስከ 20 ዓመት ያሉ የ15 ሴቶች ልብስ እና ታሪካቸው ለተመልካች ቀርቧል። ቀሚስ፣ ሹራብ፣ ጉርድ ቀሚስ፣ ...... የተቀደዱ ልብሶች በትዕይንቱ ተካተዋል። ሌላው ታሪካቸው ባጭሩ ተጽፎ ግድግዳው ላይ ይነበባል። ያንን መራር ወቅት አስታዋሽ ድባብ ያለው ፤ የእውነታውን ክስተት በምናብ ዞር ብሎ ላስታወሰ ልብ ይሰብራል ይላሉ የተመለከቱት።
ለሴት ልጅ መደፈር እንደምክንያት የሚነሳው አለባበስዋ ሊሆን እንደማይችል ለማሳየት እንደሆነ ሴታዊት የሴቶች ንቅናቄ ማሕበር መስራችና የአውደ ርዕዩ አስተባባሪ ዶ/ር ስህን ተፈራ ገልጸውልናል።  ማሕበሩ ከአራት ዓመት በፊት የተቋቋመ ሲሆን ጾታዊ ጥቃት ላይ ትኩረት አድርጎ ይሠራል። ማሕበራቸው የፆታ እኩልነትን በተመለከተ ግንዛቤ ለመፍጠር እንቅስቃሴ እንደሚያደርግም ዶክተር ስህን ይናገራሉ።
«ሴቶች መደፈር ሲያጋጥማቸው የለበሱትን ልብስ ነው የምናሳየው። ኤግዚቢሽኑ ሙሉ የልብስ ነው። 15 ሙሉ ልብሶች ነው ያቀረብነው። አብሮ ታሪኮቻቸው አለ።»
በኢትዮጵያ በአንዳንድ ቦታ የሴቶችን ክብር ዝቅ  የሚያደርጉ ልማዳዊ አስተሳሰቦች መኖራቸው ይታያል፡፡ በዚህም ምክንያት ሴቶች ለስነ-ልቦናዊ፣ አካላዊ እና ማሕበራዊ ችግሮች ተጋልጠው ይገኛሉ እንደብዙዎች አነጋገር፡፡ 
ያለእድሜ ጋብቻ እና ግርዛት የመሳሰሉ ጎጅ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ የቤት ውስጥ ጥቃት፣ ይደርስባቸዋል። የትምህርት ዕድል የማግኘት፣ እንዲሁም የንብረት እና ሃብት የማፍራት መብቶቻቸውን ተነፍገው በመቆየታቸው በማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ እንዲቀንስ አድርጓል፡፡ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶችም ከማህበረሰቡ ባህላዊና ልማዳዊ አስተሳሰቦች ጋር ተቆራኝተው ይገኛሉ። የወንዶች የበላይነት የሚንጸባረቅበትም ሁኔታ ሰፊ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ጥቃቱ ዛሬም አላቆመም ይላሉ በኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማሕበር ኃላፊ የሆኑው ወ/ት ኢየሩሳሌም ሰለሞን።
«አሁንም ቢሆን ሴቶች ተደፍረው የተለያየ ጥቃት ደርሶባቸው ወደ ማህበራችን ይመጣሉ። ይህንን ባትለብሽ ኑሮ አትደፈሪም ነበር በሚል ሴቷን ለተጨማሪ ጉዳት ሊያጋልጧት አይገባም።»
አድማጮቻችን «ምን ለብሳ ነበር» በሚል ርዕስ በአዲስ አበባ ቤተ መዘክር የቀረበው አውደ ርዕይ እስከ የፊታችን ሰኞ ድረስ እንደሚቆይ አዘጋጆቹ ለDW ገልጸዋል። እናንተም ይህን የተደፈሩ ሴቶችን እውነተኛ ስሜት ለመጋራት የሚያስችል አውደ ርዕይ በሳምንቱ መጨረሻ ልትመለከቱት ትችላላችሁ። 


ነጃት ኢብራሂም

ሸዋዬ ለገሰ

ከማዕቀፉ ተጨማሪ ዘገባዎች

ተከታተሉን