የሜርክል ፓርቲ አዲስ ሊቀመንበሩን መረጠ

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
05:29 ደቂቃ
07.12.2018

የ56 ዓመትዋ አነግሬት ክራምፕ ካረንባወር የፓርቲዉ ሊቀመንበር ሆነዋል

የጀርመኑ የክርስቲያን ዴሞክራቶች ሕብረት ፓርቲ በጀርመንኛው ምህጻሩ CDU በዛሬው ዕለቱ አዲስ ሊቀመንበሩን መረጠ። ሴዴኡ ዛሬ በሰሜን ጀርመኗ ከተማ ሀምቡርግ ላይ በጀመረው ጉባኤ ለ18 ዓመታት ፓርቲውን የመሩትን መራሂተ መንግሥት አንጌላ ሜርክልን እንዲተኩ የ56 ዓመትዋን አነግሬት ክራምፕ ካረንባወርን በሊቀመንበርነት መርጧል።

  የቀድሞው የፓርቲው የምክር ቤት ተጠሪ የ63 ዓመቱ ፍሪድሪሽ ሜርትስ እና የአሁኑ የጤና ሚኒስትር የ38 ዓመቱ የንስ ስፓን ተወዳድረው ፤ ከጉባኤተኞቹ 999 ድምጽ 450 ው ለክራምፕ ካረንባወር፣ 392 ቱ ለሜርስ ከተሰጠ በኋላ ከሁለቱ አሸናፊውን ለመለየት በተካሄደው የድምጽ አሰጣጥ ነው አሸናሪው የተለየው።  

 በዚሁ ጉባኤ መክፈቻ ላይ ሜርክል የመሰናበቻ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረኩ ሲወጡ እና ንግግራቸውንም ሲጨርሱም ጉባኤተኞቹ ለረዥም ደቂቃዎች በመቆም አድናቆታቸውን እና ምስጋናቸውን በጭብጨባ ገልጸውላቸዋል። ላለፉት 13 ዓመታት ጀርመንን የመሩት የ64 ዓመትዋ ሜርክል የመሀል ቀኙን ፓርቲያቸውን «የክርስቲያን ዴሞክራቶች ሕብረት» በፍጥነት ወደ ፖለቲካው ማዕከል ማምጣት በመቻላቸው አድናቆት ይቸራቸዋል። ለዚህም የወጣቶች ወታደራዊ እና ማሕበራዊ አገልግሎት እንዲቀር እንዲሁም ጀርመን የአቶም ኃይል መጠቀም እንድታቆም መደረጉ እና አባቶች ሕጻናት ልጆቻቸውን እንዲንከባከቡ ለማበረታት የተወሰዱት እርምጃዎች ይጠቀሳሉ። በሀገር ውስጥ አወዛጋቢ ቢሆንም ከሦስት ዓመት በፊት አንድ ሚሊዮን ስደተኞች ጀርመን እንዲገቡ መፍቀዳቸው ለሜርክል ትልቅ ቦታ ከሚያሰጡ ውሳኔዎቻቸው አንዱ ነው።

በዛሬው የመሰናበቻ ንግግራቸው የዛሬ 18 ዓመት የተረከቡት ሴዴኡ አሁን መለወጡን አስታውሰው ይህም ጥሩ ውጤት መሆኑን አመልክተዋል። በመጨረሻው የመራሄ መንግሥትነት ዘመናቸው ለፓርቲያቸው ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል።

«በሀምቡርጉ ጉባኤ አዲስ የፓርቲ አመራር እንመርጣለን። ተመራጮቹም አዲስ የፓርቲ መርሃግብር ከማውጣት ጋር ከእኔ በኋላ የሚኖረውን ሴዴኡን ዝግጁ ያደርጋሉ። በመጨረሻው የሥልጣን ዘመኔ ከብሔራዊ የፖለቲካ ሃላፊነቶቼ ጎን ለጎን ለሴዴኡ አዲስ ስኬት አስተዋጽኦ ማድረግ ለኔ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነው። እንደዚህ ነው የወደፊቱን መሠረት መጣል የምንችለው።»

ሜርክል ከፓርቲው ከሴዴኡ ሊቀመንበርነት እንደሚወርዱ ባለፈው ጥቅምት ውስጥ ነበር በይፋ  ያሳወቁት። ሆኖም እስከ ዛሬ 3 ዓመት በሚዘልቀው በመራሄ መንግሥትነት ሥልጣናቸው ላይ እንደሚቆዩ ገልጸዋል። የፓርቲው ጸሐፊ የነበሩት የ56 ዓመትዋ አነግሬት ክራምፕ ካረንባወር የአንጌላ ሜርክል የቅርብ ሰው መሆናቸው ይነገራል።

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ

ተዛማጅ ዘገባዎች

ተከታተሉን