የምዕራባዊ ሰሀራ ውዝግብ 

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
08:29 ደቂቃ
07.12.2018

የተቀናቃኞቹ ቡድኖች ልዑካን በ2019 ዓም እንደገና ለመገናኘት ዝግጁነት አሳይተዋል።

በብዛት በሞሮኮ ቁጥጥር ስር ስለሚገኘው የምዕ/ሰሀራ ግዛት የወደፊት እጣ በዚህ ሳምንት በዠኔቭ፣ ስዊትዘርላንድ የተካሄደው የ2 ቀናት ውይይት ተጠናቀቀ።  በፎስፌትና በአሳ ይዘቱ በሚታወቅ የባህር ጠረፍ ስለታደለው አወዛጋቢው ምዕ/ሰሀራ ላይ ካለፉት 6 ዓመት በኋላ ምክክር ሲደረግ ያለፈው ረቡዕ እና ሀሙስ የተካሄደው ውይይት የመጀመሪያው ነበር። 

በሰሜን ምዕራባዊ አፍሪቃ የሚገኘው 266.000 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ያለው ምዕራባዊ ሰሀራ በጎርጎሪዮሳዊው በ1975 ዓም ከስጳኝ ቅኝ አገዛዝ ከተላቀቀ በኋላ ሞሮኮ እና ሞሪታንያ ግዛቱን ግዛቱ በማለት ለቀጠሉት አራት ዓመታት ተከፋፍለው አስተዳድረውታል።  ከዚያ ሞሪታንያ ግዛቱን ከአራት ዓመት በኋላ በለቀቀችበት ወደ  ምዕራባዊ ሰሀራ «አረንጓዴ ጉዞ» ያካሄደችው ሞሮኮ ይህንኑ ደቡባዊ አካባቢ ከግዛቷ አጠቃልላ ዛሬ ድረስ  እንደተቆጣጠረችው ትገኛለች። በዚህም የተነሳ የሞሮኮን ርምጃ እንደ ወረራ የተመለከተው የምዕራባዊው ሰሀራ ህዝብን የሚወክለው በአልጀሪያ የተመለከተው የፖሊሳርዮ ግንባር ለግዛቱ ነፃነት ለብዙ ዓመታት በሞሮኮ መንግሥት አንፃር ውጊያ አካሂዶዋል።
ይኸው 15 ዓመት ሙሉ የቀጠለው ውጊያ በተመድ ሸምጋይነት በተካሄደ ድርድር እጎአ መስከረም 1991ዓም በፀና የተኩስ አቁም ደንብ አቁሞዋል፣ የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤትእጎአ ሚያዝያ 1991 ዓም ባሳለፈው ውሳኔ አንቀጽ 690 ም በሞሮኮ እና በፖሊሳርዮ መካከል የተደረሰውን የተኩስ አቁም ደንብ የሚቆጣጠር እና የምዕራባዊ ሰሀራ ሕዝብም ስለግዛቱ የወደፊት እጣ በሬፈረንደም የሚወስንበትን ሂደት የሚከታተል በምህፃሩ ሚኑርሶ የተባለ የተመድ ተልዕኮ ቢቋቋምም ውዝግቡ እስካሁን እልባት አላገኘም።  ይህ ሲታሰብ ታድያ በሰሞኑ የዠኔቭ ውይይት ላይ የተገኙት ተቀናቃኞቹ የልዑካን ቡድኖች  በጎርጎሪዮሳዊው 2019 ዓም እንደገና ለመገናኘት በመስማማት መለያየታቸውን  የተመድ ልዩ የምዕራባዊ ሰሀራ ልዑክ  ጀርመናዊው ሆርስት ከለር አስታውቀዋል።

አንድ ከፍተኛ የፖሊሳርዮ ግንባር ልዑክ፣  የሞሮኮ፣ አልጀሪያ እና ሞሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች በተሳተፉበት ውይይቱ ማብቂያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የቀድሞው የጀርመን ፕሬዚደንት ሆርስት ከለር  ይህ ውሳኔ በሞሮኮ እና ለምዕራባዊ ሰሀራ ነፃነት በሚታገለው የፖሊሳርዮ ግንባር መካከል ከብዙ አሰርተ ዓመታት ወዲህ የቀጠለውን ውዝግብ ለማብቃት የሚረዳ ትልቅ ርምጃ ነው ብለውታል።
 « ልዑካኑ ወደፊትም በዚሁ ጉዳይ ላይ ለመስራት መስማማታቸውን አስደሳች ነው። ሂደቱ የምዕራብ ሰሃራን  ወንዶች፣ ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቱን  ጥቅም  ለማስጠበቅ  እንደሚሆን ተስፋዬ ነው። ለውዝግቡ ሰላማዊ መፍትሄ ሊገን ይችላል የሚል ፅኑ እምነት አለኝ።  ልዑካኑን በጎርጎሪዮሳዊው 2019  የመጀመሪያ ሩብ ዓመት ለሁለተኛ የክብ ጠረጴዛ ውይይት ልጋብዝ  እፈልጋለሁ። »
የተቀናቃኞቹ ወገኖች አቋም እጅግ የተራራቀ በመሆኑ ታዛቢዎች ከዠኔቭ ስዊትዘርላንድ ስብሰባ ብዙም አልጠበቁም፣ ያም ቢሆን ግን፣ ተሳታፊዎች በውይይቱ ገንቢ ሀሳብ በመያዝ በግልጽ እንዲመክሩ የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተረሽ ከመማፀን አልቦዘኑም ። ይህ ልዑካኑ  ለቀጣይ ውይይት ያሳዩትን ዝግጁነት በበርሊን የሚገኘው የሳይንስ እና ፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ኢዛቤል ቤርንፌልስ እንደስኬት ተመልክተውታል። ለዚሁ ስኬትም፣ ይላሉ ኢዛቤል ቬርንፌልስ፣  አደራዳሪው ፣ እዚህ ላይ የተመድ የምዕራባዊ ሰሀራ ልዩ ልዑክ ሆርስት ከለር ወሳኝ ሚና ተጫውተዋል። 

« ሆርስት ከለር የዚህኛው ወይም የሌላኛው ቡድን ተፅዕኖ ያላረፈባቸው ገለልተኛ አደራዳሪ መሆን ተሳክቶላቸዋል። ከሳቸው በፊት ይህንኑ ኃላፊነት ይዘው የነበሩት አቻዎቻቸው አልተሳካላቸውም። እርግጥ ነው፣ ሆርስት ከለር በሌሎቹ አደራዳሪዎች አንፃር ከዚህ በፊት ይዘውት የነበረው የጀርመን  እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ መርህ ድርጅት ፕሬዚደንትነት ስልጣንም በተደራዳሪዎቹ ዘንድ ከፍተኛ ተሰሚነት እንዲያገኙ ለማድረግ ጠቅሟል። »
ለግዛቱ ሰፊ ራስ ገዝ አስተዳደር የመስጠት ሀሳብ ያቀረበችው ሞሮኮ ሀሳቧ በፖሊሳርዮ በኩል ተቀባይነት እንዲያገኝ ጥረት እንደምታደርግ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ናስር ቡሪታ አስታውቀዋል። 
«  ገላጋይ ሀሳብ ላይ ለመድረስ ከፈለግን ተጨባጩን ሁኔታ መገንዘብ ይኖርብናል። ሞሮኮ ለዚህ ዝግጁ ናት፣ የሰፊ ራስ አስተዳደር እቅድም አለ። የሚያስፈልገው የፖለቲካ በጎ ፈቃደኝ ነው፣ ይህ ከሌለ ግን የሰላሙ ሂደት አይሳካም። »
ፖሊሳርዮ ግን ከ350,000 እስከ 500,000 የሚገመቱት ሳህራውያኑ እጣቸውን በሬፈረንደም እንዲወስኑ ጥረቱን እንደሚቀጥል የፖሊሳርዮ ልዑካን ቡድን ካትሪ አዱ አስታውቀዋል።
« በሰላሙ ሂደት ለመቀጠል ዝግጁ መሆናችንን በድጋሚ እናረጋግጣለን። ሌላውም ወገን በሂደቱ ገንቢ እና ኃላፊነት በተመላው መልኩ  እንደሚሳተፍ ተስፋ እናደርጋለን። ይኸው ሂደትም ቅድመ ግዴታ ወዳላረፈበት፣  ለምዕራብ ሰሀራ ህዝብ ራሱን በራሱ የመወሰን መብት መፍትሔን ሊያስገኝ ወደሚችለው ቀጥተኛ ድርድር እንደሚያመራም ተስፋችን ነው። »
ሆኖም ለዚሁ ጥረቱ ዓለም አቀፍ ድጋፍ የሚያፈላልገው ይኸው ቡድን  በአውሮፓ ህብረት ቅር መሰኘቱን ካትሪ አዱ አክለው ገልጸዋል።

« ጉዳዩን ወደፊት ለማራመድ ጥረት በጀመርንበት ባሁኑ ጊዜ የአውሮጳ ህብረት ከሞሮኮ ጋር በአሳ ማስገሩ አጋርነት ላይ ቀደም ሲል በተደረሱ ስምምነቶች ላይ ፣ ዓለም አቀፍ ሕግን እና የአውሮጳ የፍትሕ ፍርድ ቤት ብይንን በሚጥስ መልኩ፣ እንዳዲስ መደራደር መጀመሯ አሳዝኖናል። »
የጀርመናውያኑ የሳይንስ እና ፖለቲካ ጥናት ተቋም ተንታኝ ኢዛቤል  ቬርንፌልስ የምዕራባዊ ሰሀራ ውዝግብ በተለይ አዳጋች ሆነው ያዩታል፣ ምክንያቱም ውጥረቱ በሞሮኮ እና በፖሊሳርዮ መካከል ብቻ ሳይሆን፣ በሞሮኮ እና በአልጀሪያም መካከል ነውና።
« ሁለት ውዝግቦች ተደራርበው የሚታዩበት ነው። የመጀመሪያው በሞሮኮ እና በፖሊሳርዮ መካከል ነው። ሁለተኛው በአልጀሪያ እና በሞሮኮ መካከል የሚታየው ፉክክር ነው። በሁለቱ መካከል ከፍተና ጥላቻ አለ። በምዕራባዊ ሰሀራ የተነሳ ብቻ ሳይሆን ከሰሀራ በስተደቡብ ባለው የአፍሪቃ ከፊል ተፅዕኖ የማሳረፍ፣ ማለትም ያካባቢው ኃያል መንግሥት የመሆን ጥያቄ ነው። እዚህ ላይ የድንበሩ ውዝግብም ሚና ይጫወታል። ሁለቱ ውዝግቦች ይደራረባሉ። »
የዠኔቩ ውይይት በዩኤስ አሜሪካ ግፊት እንደተካሄደ ተንታኞች ይገምታሉ። ዩኤስ አሜሪካ የተመድ ተልዕኮ፣ ሚኑርሶ  ስራውን የምዕራባዊ ሰሀራን ውዝግባ  አስቀድሞ ማብቃት ነበረበት የሚል አመለካከት ነው የያዘችው። አምስቱ የተመድ ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባል ሀገራት ውዝግቡን በተመለከተ እስካሁን አንድ አቋም መያዝ አልመቻላቸውም  ሁኔታውን እንዳወሳሰበው ይገኛል።

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ
 

ተከታተሉን