የዐቢይ ደብዳቤ ወደ የመን ሰዎች፤ ሰልፎቹ እና ቢልለኔ ስዩም

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:42 ደቂቃ
07.12.2018

የዐቢይ ደብዳቤ ወደ የመን ሰዎች፤ ሰልፎቹ እና ቢልለኔ ስዩም

በኦሮሚያ የተደረገው በመቐለ የታቀደው ሰላማዊ ሰልፍ፣ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ የመን ሰዎች የፃፉት ደብዳቤ እና ወይዘሮም ሆነ ወይዘሪት አትበሉኝ ያሉት ቢልለኔ ስዩም በሳምንቱ የሙግት መነሾ ሆነዋል።

ማኅበራዊ ድረ-ገፆች ለኢትዮጵያውያን ተጠቃሚዎቻቸው የውይይት እና የሙግት መድረክ መሆናቸውን ቀጥለዋል። ፌስቡክ እና ትዊተርን የመሳሰሉ ማኅበራዊ ድረ-ገፆች መረጃ ለማቀበል ከማገልገላቸው ባሻገር የውዝግብ እና ንትርክ መድረክ መሆናቸው አልቀረም። ሐሰተኛ መረጃዎች፣ መያዣ መጨበጫ የሌላቸው ትንታኔዎችም አይጠፉም።

የዐቢይ ደብዳቤ ወደ የመን ሰዎች

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በየርስ በርስ ጦርነት፤ የሳዑዲ አረቢያ እና አጋሮቿ ጣልቃ-ገብነት እንዲሁም በበሽታ እና ረሐብ ለምትናውዘው የመን ዜጎች የጻፉት ደብዳቤ በአንዳንዶች ለዓለም ሰላም ያላቸው ተቆርቋሪነት ማሳያ ተደርጎ ሲወሰድ ለሌሎች «የራሷ አሮባት የሰው ታማስላለች» አይነት ነገር ሆናባቸዋል።

ጠቅላይ ምኒስትሩ ባለፈው ሰኞ ኅዳር 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ የዛሬዋ ሳትሆን የቀድሞዋ የመን የነበራትን ክብር እና ሞገስ የሃይማኖት መጻሕፍት እያጣቀሱ ጭምር ዘክረዋል። የመናውያን ነበራቸው ያሉትን አንድነት ያደነቁት ዐቢይ በአገሪቱ ላለፉት ዓመታት የታየውን እና የበርካታ ዜጎችን የበላውን የርስ በርስ ጦርነት ሐራም ሲሉ ነቅፈዋል። ዐቢይ የመናውያንን ስለ ምን ሐብታችሁን ታጠፋላችሁ? አገራችሁንስ ታፈርሳላችሁ? ስልጣኔ እና ድላችሁንስ ቢሆን ሲሉ ጠይቀዋል። ዐቢይ በደብዳቤያቸው የየመን ተቀናቃኝ ወገኖች እርስ በርስ መሻኮታቸውን ትተው መፍትሔ ይፈልጉ ዘንድ ጥያቄ አቅርበዋል። በየመን ቀውስ ሳዑዲ አረቢያ እና አጋሮቿ የፈጸሙት ጥፋት ግን በደብዳቤው አልተጠቀሰም። እናም ይኸው ደብዳቤያቸው በኢትዮጵያውያን ዘንድ የመወያያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል።

አሚር ኑር የተባሉ የፌስቡክ ተጠቃሚ "ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አህመድ የሚያስበውና የሚጨነቀው ስለሀገር ብቻ ሳይሆን ስለዓለምና ስለሰው ልጆች ነው። ዛሬ ዶ/ር ዐቢይ የመን ከገባችበት ከባድ ቀውስ እንድትወጣ ብሎ ለየመን ተዋጊዎች ምክር አዘል አስታራቂ ደብዳቤ ልኳል። እንዲህ ያለ ሰፋ ያለና ያማረ አሰተሳሰብ ያለው አርዓያ ሰው ስለሰጠን ፈጣሪ ይመሰገን" ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

አገው ዩኒቲ ፕሬስ የተባለ የፌስቡክ ገፅ ግን ደብዳቤውን መሠረት አድርጎ ጠቅላይ ምኒስትሩ ላይ የሰላ ትችት ሰንዝሯል። አጠር ያለው ጽሑፍ ሲጀምር «የምትመራው ሕዝብ እየተጨፈጨፈ ትንፍሽ ሳትል ስለ የመን ትጨነቃለህ?» ሲል ያጠይቃል።

«ዐቢይ አህመድ አታፍርም ወይ? ባንተ የስልጣን ዘመን ሰው በአደባባይ ተወግሮ እየተሰቀለ፡ ወገን ወገኑን በዘር ለይቶ የሚገድልበት አገር መሪ ሆነህ ሌሎች አገሮችን ስለ ሰላም ለመስበክ እንዴት ደፍርክ? ገመናህ አያሳፍርህም? በየቀኑ ግድያና ግፍ የሚፈፀምበትና በየቀኑ የሚተራመስ አገር እየመራህ ስለ የመን ችግር ታወራለህ? ከማውራትህ በፊት የራስህን ሕዝብ ሰላም ለማስጠበቅ ለምን አትሰራም? የምትመራት አገር በእጅህ ልትበታተን ጫፍ መድረሷ እንዴት አልታይህ አለሲል አስተያየቱን ጽፏል።

ኢብራሒም አብዱረሕማን የተባሉ ሰው በአረብኛ የተፃፈውን የዚሁ ደብዳቤ ቅጂ በፌስቡክ ገፃቸው ለጥፈው "ለየመን ሕዝብ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተላከ መልዕክትን ተመለትኩኝ:: የአረብኛው ትርጉም ላይ የዐቢይ ሥም አሊይ አህመድ አብይ ተብሎ ነው የተፃፈው:: የተርጓሚው ስህተት ይታያል ምክንያቱም በአረብኛ የሥም አደራደር ለውጥ የለም" ሲሉ የተመለከቱትን ጉድለት ለመጠቆም ሞክረዋል።

የሰላማዊ ሰልፎቹ ነገር- ኦሮሚያ እና ትግራይ

በኦሮሚያ እና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች በተፈጠረ ግጭት የሰው ሕይወት ከጠፋ በኋላ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ሲደረጉ ሰንብቷል። ተቃውሞዎቹ በተደረጉ ማግሥት የተጀመረው የማኅበራዊ ድረ-ገፆች ውይይት እና ሙግት ሞቅ ደመቅ ብሎ ነበር። ዋነኛው የሙግት ማዕከል የተቃውሞ ሰልፎቹ አስፈላጊነት ነበር። የሐረርጌው ጸሐፊ አፈንዲ ሙተቂ በጉዳዩ ላይ ያለውን አስተያየት በግል የፌስቡክ ገጹ ሲያካፍል ለኦሮሞ ወጣቶች ያለውን መልክት በማስተላለፍ ጀምሯል። አፈንዲ  "እስቲ ረጋ በሉ። ሰከን በሉ። ያደረጋችኋቸው ሰልፎች ዓላማቸውን አሳክተዋል። ስለዚህ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ ተንተርሶ ሥራውን እንዲሠራ ዕድል ስጡት። ያለው መንግሥት ለራሱ በብዙ ሳንካዎች የተወጠረ መሆኑን እናውቃለን። ስለዚህ እርሱ ከሚሠራው ሥራ ግማሽ ያህሉን መሥራት ያለብን እኛ ነን። " ብሏል። "የኔና የመሰሎቼ ፍላጎት መንግሥትን መወጠር አይደለምየሚለው አፈንዲ "የኛ ጥያቄ መንግሥት ልሒቃን ከሚባሉት ጥቂት ግለሰቦችና የፖለቲካ መሪዎች በፊት ሕዝቡን ያስቀድም ነው። ሕዝብ እየተማረረባቸው ያሉትን የጸጥታ፣ የመልካም አስተዳደርና የኢኮኖሚ ችግሮችን ችላ ብሎ በገፅታ ግንባታ ላይ ብቻ ማተኮሩን ያቁም ነው። ኸላስ!!" የሚል አስተያየት አለው። ጸሐፊው "ሰልፎቹ መካሄዳቸው ተገቢ ነው። ነገር ግን ከዚህ በኋላ ሰልፍ ማድረጉ ቆሞ ወደ ሰላማዊ መፍትሔ ፍለጋ ብንሄድ ይሻላል"  ሲል ይቀጥላል። "ሕዝቡ ወያኔ ይመለስ» እያለ አይደለም። ስለዚህ ወያኔዎችንና ደጋፊዎቻቸውን ለማሳፈር ስንል ሰልፉ ቢቆም ይሻላል" ሲል የጻፈው የሐረርጌው "መንግሥት ሆይ- አንተም ነቃ በል! ቶሎ ተንቀሳቀስ! ሕዝቡ ካንተ የሚፈልገው ድርጊት ነው። ድርጊት!" የሚል መልዕክቱን አስተላልፏል።

ዘ-ፊንፊኔ ኢንተርሴፕት የተባለው የፌስቡክ ገፅ በኦሮሚያ የተካሔዱትን ሰልፎች አስመልክቶ ሰፋ ያለ አስተያየት አስፍሯል። ገፁን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው ወገን ማንነት ባይታወቅም በክልሉ እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ያተኮሩ መረጃዎች እና አስተያየቶች በገፁ ሲያጋራ ይስተዋላል።

ዘ-ፊንፊኔ ኢንተርሴፕት "ሰሞኑን በኦሮሚያ በተደረጉት ሰልፎች ሕዝቡ መነሳት ያለባቸውን ጥያቄዎች በሙሉ በሚገባ አንስቷል። በተለይ በምዕራብ ኦሮሚያ እየጠፋ ያለው የሰው ሕይወት በጣም የሚያስቆጭም የሚያናድድም ነው። መንግሥት ጉዳዩ ላይ ቸልተኛ መሆንም፤ ቸልተኛ መስሎ መታየትም የለበትም። ወደ 17 አካባቢ የሚጠጉ የኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ሕግን በማስከበር ላይ እያሉ በተገደሉ በሁለተኛው ወይም በሦስተኛው ቀን የስንዴ ማሳ ለመጎብኘት ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ ፕሬዚደንት ለማ ወደ ጅሩ መሄዳቸው ግራ ያጋባል። እንደዚህ አይነት ጉብኝቶች ቀድመው የሚያዙ ቢሆንም መሰረዝ ይቻል ነበር። የሰልፈኞቹ ጥያቄዎች ተገቢና የኦሮሚያ ክልል መንግሥትም ሆነ የፌዴራሉ መንግሥቱ አፅንኦት ሰጥተው ሊሰሩባቸው የሚገቡ ናቸው። አሁን ይሄንን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል። ቃል መግባት ብቻ ሳይሆን በቤኒሻንጉልና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች መከላከያ ኃይሉ ተንቀሳቅሶ የሰዎችን ደህንነት እንዲያረጋግጥ ወስነዋል" የሚል አስተያየት በገፁ አስፍሯል።

"ነገር ግን" ይላል የዘ-ፊንፊኔ ኢንተርሴፕት አስተያየት "ነገር ግን አሁንም ሰልፉ ቀጥሎ መስቀል አደባባይ ጭምር መደረግ አለበት የሚሉ አሉ። ምን ተጨማሪ ትርፍ እንደሚኖረው ግን ግልፅ አይደለም። ሰልፉ ቢደረግ ሊገኝ የሚችለው ጥቅም በመንግሥት ተደማጭነት ማግኘት ነው። እሱን ደግሞ ባለፉት ጥቂት ቀናት የተደረጉት ሰልፎች አሳክተውታል። ሰልፉ ሊኖረው የሚችለው የሚኖረው ጉዳት ደግሞ ግልፅ ነው። ሰርጎ ገቦች ሕዝቡ ላይ ጉዳት ለማድረስ ወይም ግጭት የሚቀሰቅስ ነገር ለማስተላለፍ ሊጠቀሙበት ይችላሉ" የሚል ሥጋት እንዳለ ጭምር አትቷል።

በትግራይ ክልላዊ መንግሥት መቀመጫ መቐለ ነገ ቅዳሜ ሰላማዊ ሰልፍ ሊደረግ ታቅዷል። የክልሉ መንግሥት ለተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የጻፈው ደብዳቤ እንደሚጠቁመው የነገው ሰልፍ "ሕገ-መንግሥታችን ይከበር። ፍትኅ በሁሉም ይንገሥ" በሚል መፈክር ይካሔዳል። ለሰልፉ የተደረጉ ቅድመ-ዝግጅቶችን የሚጠቁሙ ፎቶግራፎችም በማኅበራዊ ድረ-ገፆች ሲዘዋወሩ ታይተዋል። ዘ-ፅዓት ሴቭአድና አናንያ የተባሉት የፌስቡክ ተጠቃሚዎች በግል የፌስቡክ ገፃቸው "መቐለ ለቅዳሜው መሬት አንቀጥቅጥ ሰላማዊ ሰልፍ ዝግጅቷን ጨርሳለች" ሲሉ ፅፈዋል። በሰላማዊ ሰልፉ ትግራይ "ከሌሎች በእኩልነትና በመከባበር አብሮ ለመኖር ፍላጎቱ ካላቸው ሕዝቦች ጋር በመፈቃቀድ ለመኖር ያላትን ዝግጁነት ትገልፃለች፤ በአስር ሺዎች መስዋእትነት የተተከለውን ፌደራላዊ ስርዓት እንዲፀና፣ ሕገ-መንግስቱ በምሉእነት እንዲከበር ትጠይቃለች፤ የሕግ ጥሰቶች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የሕዝቦችን መፈናቀልና ግድያ ታወግዛለች፤ ማንነትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች ታወግዛለች፤ የትግራይ ሕዝብን ለመደፍጠጥ እየተደረጉ ያሉ ሴራዎችን ታወግዛለች ፤ ሁሉንም ጥቃቶች አሸንፎ ለመውጣት ያላትን ቁርጠኝነትም ታሳያለች" የሚል መረጃ ዘ-ፅዓት ሴቭአድና አናንያ በፌስቡክ ገፃቸው አስፍረዋል። ልሳን ተጋሩ የተሰኘ ገፅ ካሰፈረው መረጃ መካከል "የትግራይ ሰላማዊ ሰልፍም ከህወሀት ጥንካሬ ጀርባ ትክክለኛ ስርአት ሕዝብ መፈጠሩን የሚያመላክት የፖለቲካ መገለጫ ነው" የሚለው ይገኝበታል። በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት ሳቢያ እንደ ኦሮሚያው ሁሉ የመቐለውን ሰልፍ በዓይነ ቁራኛ ያዩት አልጠፉም። አወቀ አብርሐም ግን "መቐለ ላይ ሰልፍ መውጣት ለምን እንደ ተዓምር ይታያል? ሰልፉ ላይ የሚነሱ ሃሳቦች ላያሳምኑን ይችላሉ ግን ከኛ የተለየ ሃሳብ እንዲንሸራሸር መፍቀድ የዲሞክራሲ ሀ ሁ ይመስለኛል:: ሰላማዊ ሰልፍ መውጣት የዜጎች መብት ነው! መቀለ-ባህር ዳር-አምቦም ይሁን አዲስ አበባ ላይ!" የሚል ዕምነታቸውን በግል የፌስቡክ ገፃቸው አጋርተዋል።

ወይዘሮም ሆነ ወይዘሪት አትበሉኝ!

በጠቅላይ ምኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕረስ ሴክሬታሪ ሆነው በማገልገል ላይ የሚገኙት ቢልለኔ ስዩም ለጋዜጠኞች ወይዘሮም ሆነ ወይዘሪት አትበሉኝ ማለታቸው በማኅበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ መነጋገሪያ ርዕሰ-ጉዳይ ሆኗል።  ከጠቅላይ ምኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ደርሶኛል ብሎ መረጃውን በግል የፌስቡክ ገፁ መጀመሪያ ያጋራው ጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ለጋዜጠኞች የተላከ ተመሳሳይ መልዕክት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሲዘዋወር ታይቷል። ሴታዊት የተባለው እና የሴቶች ዕኩልነት እንዲከበር የሚወተውቱ መረጃዎች የሚያሰራጨው ገፅ ድጋፋቸውን ከገለጹ መካከል ይገኝበታል። ገፁ "እንደ ሴታዊት ንቅናቄ ቢልለኔ ስዩም ወይዘሮ ወይም ወይዘሪት የሚሉትን ቅጥያዎች አልፈልግም በስሜ ብቻ ጥሩኝ ያለችውን እንደግፋታለን! ጉዳዩም የፌሚኒስት አጀንዳ እንደሆነ እናምናለን:: ወይዘሮ ወይም ወይዘሪትን ላለመጨመር መወሰኗ ግላዊ መብቷ ነው! ሆኖም እንደ ሴታዊት በጣም የምናምንበት እናም የምንጠቀምበት ነገር ነው:: ወይዘሪት ወይም ወይዘሮ አንድ ሴት ማግባት አለማግባቷን ለማሳየት የሚሰጥ ማዕረግ ነው:: ወንድ ግን አቶ መባል ከጀመረ ጀምሮ በማግባት ባለማግባቱ በስሙ ቅጥያ ላይ የሚደረግ ለውጥ የለም:: የጋብቻ ሁኔታ እንደመጠሪያ መጠቀምን አለመፈለግ መብት ነው፤ መብቷም ሊከበር ይገባል" የሚል መልዕት አስፍሯል።

የትዊተር ተጠቃሚዋ ሐቢባ ባሕሬ አብደላ "ጓዶች! የቢልለኔ ስዩምን መልእክት ሰማን አይደል? /ሮ ወይም ወ/ት ብላችሁ አትጥሩኝ ስሜን ተጠቀሙ ብላናለች። እኔንም እንደዛው። የትዳር ሁኔታዬ የራሴና የራሴ ጉዳይ ብቻ በመሆኑ በስሜ እንድትጠሩኝ ይሁን" ብላለች። ሐቢባ በዛው በትዊተር ገጿ ከሌሎች ሰዎች ጋር ባደረገችው የመልዕክት ልውውጥ "ለሰው ስታስተዋውቁኝም የእከሌ ሚስት(ባለቤት) ሳይሆን እከሊት ብላችሁ ይሁን" የሚል ሐሳብ ጭምር አስፍራለች። በለው የኔዓለም የተባሉ የትዊተር ተጠቃሚ ለሐቢባ በሰጡት ምላሽ "አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ አሉ! ሴታዊነት/feminism ጭፍን ያደርጋል መሰለኝ :: የወንድ ጥላቻም ይንጸባረቅበታል:: የጾታ ልዩነትን ከፍ አድርጎ በማጉላት ወደ አጉል ባሕል ይከታል:: ለእኩልነትና ለመብት እንደ ሰው መታገል ነው የሚመከረው" የሚል ሐሳብ አስፍረዋል።

ጌቱ ካዋቱ ደግሞ ጋዜጠኛ ኤልያስ መሠረት ባሰፈረው መልዕክት ሥር "ያገባና ያላገባ ወንድ የሚለይ ማዕረግ የለም፤ ለምን ለሴቶች ብቻ?" ሲሉ ጠይቀዋል። ኢሳያስ መኩሪያ "በተደጋጋሚ በድረ-ገፅ መገናኛ መሥመራቸው ለተላኩላቸው ጥያቄዎች አንድ መሥመር መልስ ለመመለስ ጊዜ ያጡት እኚህ ሴት ከስማቸው በፊት ስለሚጠቀስ የማዕረግ መጠሪያቸው ይህን ያህል ትኩረት ሰጥተው መከታተላቸው ሳያንስ እንዲህ ብላችሁ እንጂ እንዲያ ብላችሁ አትጥሩኝ ብለው መልዕክት ለመላክ ጊዜ ያላቸው መሆኑ ይገርማል፡፡ ዘንድሮም ገና አፍ አንጂ ጆሮ እዚያ አራት ኪሎ ግቢ አልገባም ማለት ነው?" የሚል አስተያየታቸን ጽፈዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠተዛማጅ ዘገባዎች

11:08 ደቂቃ
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | 03.09.2018

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

09:14 ደቂቃ
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | 04.01.2019

ከሰሞኑ፦ የፕሬስ ሴክረተሪ ሹመት አነጋግሯል

ተከታተሉን