ድምፃዊ አቡሎ ጡሞሮ ሲታወስ

አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:52 ደቂቃ
09.12.2018

ድምፃዊ አቡሎ ጡሞሮ ሲታወስ

ድምፃዊ አቡሎ ጡሞሮ የደቡብ ክልል ካፈራቸዉ የባህል ድምፃዉያን መካከል አንዱና አንጋፋዉ ነዉ። ድምፃዊዉ ምንም እንኳ ሙያዉ ከጥበብ ጋር የተገናኘ ባይሆንም ከ30 ዓመታት በላይ የተለያዩ የባህል ዜማዎችን በመድረክ ተጫዉቷል።

ትዉልድና እድገቱ በደቡብ ብሄር ብሄሮችና ህዝቦች ክልል በሀዲያ ዞን በአሁኑ ሶሮ ወረዳ በቀድሞዉ አጠራር ጠምባሮ ወረዳ አድጊደጊ ቀበሌ ነዉ። የጥበቡን ዓለም የተቀላቀለዉም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን እየተከታተለ ባለበት ወቅት ነዉ። እዚያዉ የትዉልድ ቀየዉ የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት እያለ። በአብዛኛዉ ህዝብ ዘንድ የሚታወቅበትንና አብሮነትን ፍቅርን በሚሰብክ ጭፈራ የታገዘዉን «ቦያ ሰለሜ» ዜማን መጫወት የጀመረዉም በዚሁ የልጅነት እድሜዉ የቀበሌ ኪነት ዉስጥ ነበር ይላሉ፤ የድምፃዊዉ የቅርብ ዘመድና አብሮ አደግ አቶ አሰፋ ሎምቤሶ።
የአዉራጃ ኪነት ዉስጥ በድምፃዊነትና በተወዛዋዥነት እየሰራ ትምህርቱን ጎን ለጎን ይከታተል የነበረዉ ድምፃዊ አቡሎ ጡሞሮ የ12 ኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በሆሳዕና ከተማ ንግስት እሌኒ መሀመድ ሆስፒታል ነበር ተቀጥሮ መስራት የጀመረዉ። ከዚያም የመጀመሪያ ዲግሪዉን በሂሳብ መዝገብ አያያዝ በማጠናቀቅ የሀዲያ ዞን ፋይናንስን ጨምሮ በተለያዩ መስሪያ ቤቶች በኦዲተርነት ሰርቷል። ያም ሆኖ ግን ከሚወደዉ የሙዚቃ ስራዉ አልተለየም ነበር። ድምፃዊዉ ስራዎቹን በካሴት አሳትሞ ለህዝብ ጀሮ ባያበቃም ከሀድያ የባህል ቡድን ጋር በመሆን በህዝብ ዘንድ የሚታወቅበትን «ሰለሜ ሰለሜ »ዜማን ጨምሮ  በርካታ የሀድያ ባህላዊ ዜማዎችን ላለፉት 38 ዓመታት በተለያዩ መድረኮች ሲያቀርብ ቆይቷል። 
በሀድያ ዞን የባህልና ቱሪዝም  የቋንቋና ሥነ-ጥበብ  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አርሰዴ አንተሲ ከድምፃዊ አቡሎ ጡሞሮ ጋር ለበርካታ ዓመታት አብረዉ ሰርተዋል።« አቡሎ የሀድያ የባህል አምባሳደር ነዉ» በማለት ይገልፁታል።
«አቡሎ በግል ስብዕናዉ ሳቂታ፣ ተጨዋች፣ ተግባቢና የሚወደድ ባህሪ ነበረዉ » የሚሉት አቶ አሰፋ ሎምቤሶ በበኩላቸዉ ለረጅም አመታት የሀድያን ባህልና ወግ ከማስተዋወቅ አንፃር የነበረዉ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ እርሱን ማጣት እንደ ቤተሰብም እንደ ሙያ አድናቂም ትልቅ የባህል ቅርስ ማጣት መሆኑን ይናገራሉ።
ድምፃዊዉ ባለትዳርና የ 5 ልጆች አባት ሲሆን ላለፉት ሁለት ወራት በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ህዳር 15 ቀን 2011 ዓ/ም በተወለደ በ 56 ዓመቱ በሆሳዕና ከተማ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። ለነብሱ እረፍትን ለቤተሰቡ መፅናናትን እንመኛለን።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ

ሸዋዬ ለገሰ 

ተዛማጅ ዘገባዎች

ተከታተሉን